ከልካይ ያጣው በሥልጣን ያላግባብ መጠቀምና አስመሳይነት

 ethiopian human right commussion
October 2023

by voice of fano

የቁጥጥር ሥርዓቱ በደከመ መንግሥት ውስጥ ሌብነት፣ አጭበርባሪነት፣ አድሏዊነት፣ ተውሳክነት (ጥገኝነት)፣ ከሃዲነት፣ አስመሳይነት፣ ጉቦኝነት፣ ሙሰኝነት ተስፋፍቶ ሊገኝ ይችላል፡፡ መንግሥቱ እየተዳከመ በሄደ መጠን የመቆጣጠር አቅሙ እየቀነሰ ስለሚሄድ የተጠቀሱት ማኅበራዊ ቀውሶች እያደጉ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ መማረር ይጀምራል፡፡ ለመሆኑ ሌብነት፣ ሙሰኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ብልሹ አስተዳደር፣ የውሸት ባለሥልጣንነት ስንል ምን ማለታችን ነው? በዚህ ጽሑፍ ጽንሰ ሐሳቡን ቀለል ባለ መንገድ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ጽሑፉ የተጻፈበት መሠረታዊ ምክንያት በአገራችን ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና አሳታፊነት የሰፈነበትን ሥርዓት ለማስፈን ምን መደረግ እንዳለበት አነስተኛ ሐሳብ ለመሰንዘር ያህል ነው፡፡ ሌባ ባለሥልጣን ማለት በቀጥታ የሰው ኪስ ወይም መጋዘን፣ ወይም ባንክ ገብቶ የሚሰርቅ አይደለም፡፡ ሌባ ባለሥልጣን ማለት በተለይም በመንግሥት እምነት ተጥሎበት፣ የተጣለበትን እምነት አሽቀንጥሮ በመጣል የመንግሥትን ሀብት ለራስ ጥቅም ለማዋል ከስፒል ጀምሮ በሚሊዮኖች እስከሚቆጠር ድረስ የሚሰርቅ ማለት ነው፡፡ በቢሮ እንዲጽፍበት የተሰጠውን እስክሪብቶ ለሌላ መሥሪያ ቤቱ ለማይመለከተው ሰው የሰጠም ከሌባ ይመደባል፡፡ ለሥራ የተሰጠውን መኪና አሥር ሜትር ተጉዞ እንኳን ቢሆን ለመንግሥት አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር ለግሉ ጥቅሙ ከተጠቀመበት ያው ሌባ ነው፡፡ ለሥራ የተሰጠውን ላፕቶፕ ወይም ሌላ ነገር ለልጁ፣ ለጓደኛው፣ ለወዳጁ የሰጠም ያው ሌባ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌባ ባለሥልን የግል ጥቅሙን ለማካበት ሲል ሥልጣኑን በመጠቀም፣ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የጥበቃ ኃይል በማዘጋጀት፣ ልዩ ልዩ ሕጋዊ ሽፋኖችን በመስጠትና ሕጋዊ በማስመሰል የኮንትሮባንድ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸው ሌባ ባለሥልጣን ሁሉም ነገር የእሱ አይደለምና መረጃ እንዳይገኝበት ማንኛውንም ሰነድ ድምጥማጡን ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ብዙውና ትልቁ ሌብነት ሰነድ በመሰረዝ፣ በመደለዝ፣ እስከ ጭራሹም በማጥፋት የሚከናወን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ከማጭበርበር ጋር የሚያያዝ ይሆናል፡፡ ረቀቅ ያለው ሌባ ባለሥልጣን ሥልጣኑን በመጠቀም የመንግሥትን ንብረትን ከቀላል እስከ ውስብስብ ዘዴዎችን በመጠቀም ጭምር ወደ ግል ንብረትነት ሲቀይር የሚገኝበት ሁኔታም አለ፡፡ እንዲህ ያለው ሌባ ባለሥልጣን የሌብነት ተግባሩን የሚያከናውነው እጅግ በተራቀቀ ዘዴም ሊሆን ስለሚችል ሕገወጥ ተግባሩ ሕጋዊ እስኪመስል የተራቀቀ ነው፡፡ ሌባ ባለሥልጣን በቀጥታ ራሱን ተሳታፊ በማድረግ ሳይሆን በእጅ አዙርና በሥውር የጨዋዎች ጨዋ በመምሰልም ሊመነትፍ ይችላል፡፡ ሌባ ባለሥልጣን ከብዙዎች ጋር ይወዳጃል፡፡ ይህ ሰው የሚፈልገውን እስኪያገኝ ድረስ በብዙ ሰዎች ዘንድም ጥሩ፣ የዋህ፣ ታማኝ፣ ቃሉን የሚፈጽም መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ዊልያም ፒት የተባለው እንግሊዛዊ መስፍን (1708 እስከ 1778)፣ «ወሰን የሌለው ሥልጣን የባለሥልጣናትን አመለካከት እንደ ብል ወይም ምስጥ እንክት አድርጎ የሚበላ ሲሆን፣ ይህም የሕጋዊ ሥርዓት ማክተሚያ የሕገወጥነት መጀመርያ ይሆናል፤» ሲል ይገልጸዋል፡፡  አሁን ኢትዮጵያ ላይ የምናያቸው ባለስልጣናት ከላይ ከተቀስኩአቸው ነገሮች በላይ ብዙ ነገሮችን አንደሚያደርጉ የሚታይ ሀቅ ነው::